ሰግላ · ከለላ · ወሎ
ፅንሰትና ልደት
በቤተ አምራ (አሁን ወሎ) በከለላ ወረዳ ሸግላ (ሰግላ) ተወለዱ። በጥቅምት 3 ቀን 1357 ዓ.ም ተፀንሰው፣ በሐምሌ 7 ተወለዱ። አባታቸው ሕዝበ ጽዮን — የቤተ መንግሥት ባለሟል፣ ጠቢብና የሰግላ ሀገረ ገዥ — እናታቸውም እምነ ጽዮን ናቸው። ሁለቱም እንደ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ በእግዚአብሔር ሕግ ጸንተው ሲኖሩ ልጅ አልነበራቸውም። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከመልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ጋር ተገልጻ ጸሎታቸውን ተቀብላ የተባረከ ልጅ እንደሚወልዱ፣ ስሙንም እንደ ሰማእታት አለቃ ቅዱስ ጊዮርጊስ «ጊዮርጊስ» እንዲሰይሙ አዘዘቻቸው።









